የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማህበራት ፌዴሬሽን (ፊፋ) ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው “ከፍተኛ የፊፋ ዳኝነት ኢንስትራክተሮች” ስልጠና በአዲስ አበባ በመሰጠት ላይ ነው፡፡

ነሐሴ 29/2009 ዓ.ም በካፒታል ሆቴል በተጀመረው የስድስት ቀናት ሥልጠና ዋና ዓላማ ለዓለም አቀፍ እግር ኳስ ውድድሮች ብቃት ያላቸውን ዳኞች ለማፍራት የወሳኝነት ሚና የሚጫወቱ ኢንስትራክተሮች ማብቃትን መሰረት ያደርጋል፡፡

በኮርሱ መክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የካፍ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የአርቢትሮች ኮሚቴ ሰብሳቢ ሚ/ር ሱሌይማን ዋቤሪ ባደረጉት ንግግር የእግር ኳስ ዳኞችን ውድድር የመምራት አቅም ለማጐልበትና ወጥነት ያለው የህግ አተረጓጐም በሁሉም ውድድሮች ሥራ ላይ እንዲውል ለማስቻል የኢንስትራክተሮችን አቅም መገንባት ወሳኝነት እንዳለው አስምረውበታል፡፡ ኢንስትራክተሮችን ማብቃት ትክክለኛ ውሳኔ በመስጠት ውድድሮቻችን በተገቢው መንገድና በጥራት ከመምራት ባሻገር ለእግር ኳስ ስፖርት እድገት፣ ውበትና ጤናማ ፉክክር ዋነኛው መሰረት እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

ስልጠናው በከፍተኛ የፊፋና ካፍ አምስት ሙያተኞች አማካኝነት እየተሰጠ ሲሆን ከ28 የአፍሪካ ሀገሮች የተውጣጡ ከ50 በላይ የዳኝነት አካል ብቃትና የቴክኒክ ኢንስትራክተሮች ተካፋይ ሆነውበታል፡፡ ኢትዮጵያ የስልጠናው አስተባባሪና አዘጋጅ በመሆንዋ ሦስት ኢንስትራክተሮች በኮርሱ የማሳተፍ እድል አግኝታለች፡፡

የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ መምሪያ ተሳታፊዎች ፈጣን የቪዛ አገልግሎት እንዲያገኙ ያደረገው ትብብርና የሰጠው ድጋፍ ሀገራችን  ከሌሎች ሀገሮች በቀዳሚነት ኮርሱን እንድታስተናግድ ያስመረጣት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ሁለት ዓለም አቀፍ የሙያተኞች ሥልጠናዎች በአዲስ አበባ ያካሄደው ፊፋ በ2010 ተጨማሪ ሰልጠናዎችና ስብሰባዎች በአዲስ አበባ እንደሚያዘጋጅ ይጠበቃል፡፡ በተጨማሪም ፊፋ በአዲስ አበባ አህጉራዊ ጽህፈት ቤት የመክፈት እቅዱ ከተሳካ ሀገራችን በርካታ የፊፋና የካፍ ስብሰባዎችና ስልጠናዎች ለማስተናገድ የተሻለ እድል ይኖራታል፡፡

አጋራ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል ነው። በ1943 እ.ኤ.አ. የተመሠረተ ሲሆን፣ በ1953 እ.ኤ.አ. የፊፋ፣ እንዲሁም በ1957 እ.ኤ.አ. የካፍ (CAF) አባል ሆነ። ይህ አካል የብሔራዊ እግር ኳስ ሊግን እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድንን ያቀናጃል።

ምላሽ ይተው

Please enter your comment!
Please enter your name here