የጀርመን ቡንደስ ሊጋ ተሳታፊ አንጋፋው እግር ኳስ ክለብ ባየርሙኒክ አመራር አዲስ አበባ ውስጥ የእግር ኳስ ትምህርት ቤት ለመክፈት እና በእግር ኳስ ስፖርት ልማት ላይ ለመስራት ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በቅድመ ሁኔታዎች ላይ ለመምከር ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ ፡፡ 

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከጀርመን መግንሥት ጋር ባለው ዘርፈ ብዙ የዲኘሎማቲክ ግንኙነት ውስጥ አንዱ ስፖርት በመሆኑ ቀደም ባሉት ጊዜያትም ኢትዮ ጀርመን የእግር ኳስ ልማት በሚል ዳይሬክተር የነበሩትን ሚ/ር ፊከርት ወደ ኢትዮጵያ በመላክ የተለያዩ ስፖርታዊ ሥራዎች የተሰሩ ሲሆን የቆይታ ጊዜያቸው በማለቁ የታቀዱት ኘሮጀክቶች ሳይጠናቀቁ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡

ይህንን ኘሮጀክት በተመለከተ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከነበሩት የጀርመን አገር ኘሬዚዳንት ፀሐፊ ጋር ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ ዶ/ር ኢያሱ መርሃጽድቅ እና ከቴክኒክና ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ኩሩ በአዲስ አበባ ስታዲየም በአደረጉት ቆይታ፤ ኘሮጀክቱ ለአገራችን እግር ኳስ ስፖርት በእጅጉ አሰፈላጊ እንደሆነ በገለፁላቸው መሠረት የጀርመን መንግሥት ከሚ/ር ፊከርት ጋር የባየርሙኒክ ክለብን በማነጋገር ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ቀደም ሲል የተጀመረው ኘሮጀክት የሚቀጥልበትን ሁኔታዎች ለመፍጠር የታቀደ ነው፡፡

በአዲስ አበባ በሚያደርጉት ቆይታ ለየት ያለ የአንድ ቀን የእግር ኳስ ውድድር እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች በሆኑ በአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስር ውድድራቸውን እያካሄዱ ባሉ በ8 ክለቦች  መካከል ሚያዚያ 9 ቀን 2011 ዓ.ም ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡ ዓላማውም የባየርሙኒክ እግር ኳስ ክለብ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊከፍት ለአቀደው ት/ቤት መልካም እይታ እንዲኖረው፣ የእግር ኳስ ተጫዋቾቻችን የኳስ ብቃት ምን ያህል ነው የሚለውን ለማሳየትና ግንዛቤ ለማስጨበጥ በዚህ መልኩ ስዕላዊ እይታን ለመፍጠር የታሰበ ነው፡፡ 

በትላንትናው እለት ሚያዚያ 2 ቀን 2011 ዓ.ም የቅድመ  ውድድር ልምምድ በአዲስ አበባ ስታዲየም  ሙሉውን ሜዳ ግማሽ ግማሽ በማድረግና የሜዳውን ሁኔታ እና የጨዋታውን ሂደት እንዲያውቁት በሚል በግማሽ ግማሽ ሜዳ እንዲጫወቱ የተደረገ ሲሆን በጣም ጥሩ እና የሚስብም ነበር፡፡ በዚህም የቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ኢትዮጵያ መድን፣ የጋዜጠኛ ሰይድ ኪያር ሰላም እግር ኳስ ክለብ  እንደዚሁ ፍቅረ ሠላም የሚባሉ የታዳጊዎች ቡድን መካከል ጨዋታው ተካሂዳል፡፡

በዚም መሠረት አንዳድ መስተካከል የሚገባቸው ነገሮችን ለመመልከት የቻልን ሲሆን አንዳንዶቹ ተሳታፊዎች እድሜያቸው ዝቅተኛ በመሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ጠንከር ጠንከር ያሉ በመሆናቸው ለታሰበው ውድድር ለማካተት አስቸጋሪ ሆነው አግኝተናቸዋል ፡፡ እንደመፍትሔም ለአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የመከላከያ እና የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥያቄ የአቀረብን ሲሆን እንዲሁም የኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው  እና የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ቡድኖች እንዲሳተፋ እናደርጋለን፡፡ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከኛ ጋር በመሆን ስራዎችን እየሰራ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቴክኒክ ዳይሬክተር ኢንስትራክተር መኮንን ኩሩ ገልጸውልናል፡፡

በዕለቱ የክብር እንግዶች በተጋባዥነት የሚገኙ ሲሆን የተለያዩ መስተንግዶዎች የሚኖሩ ይሆናል፡፡  

ባየርሙኒክ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ለመሥራት ለአሰባቸው ሥራዎች በትናንትናው ዕለት ከጀርመኑ የባህል አታሼ ሚ/ር ስቴፈን ጋር በመሆን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተሰጠውን የካፍ አካዳሚ የጐበኙ ሲሆን አካዳሚውን ወደ ሥራ ለማስገባት ባየርሙኒክ ፍላጐቱን ገልፆል፡፡

በአጠቃላይ ባየርሙኒክ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱ በእግር ኳሳችን እድገት ላይ ምልካም እድል የሚፈጥር ነው ብለን እናምናለን፡፡ በተጨማሪም ይህንኑ ሁኔታ ለማስኬድ የሚያስችለውን ረቂቅ የመግባቢያ ሰነድ የተላከልን በመሆኑ በረቂቁ ላይ የተቀመጡ ነጥቦችን በጥልቀት በመመርመር ለእግር ኳሳችን እድገት አመቺ በሆነ መልኩ የሚሠራበት መንገድ ይመቻል ሲሉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክና ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኢንስትራክተር መኮንን ኩሩ ገልፀውልናል፡፡  

አጋራ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል ነው። በ1943 እ.ኤ.አ. የተመሠረተ ሲሆን፣ በ1953 እ.ኤ.አ. የፊፋ፣ እንዲሁም በ1957 እ.ኤ.አ. የካፍ (CAF) አባል ሆነ። ይህ አካል የብሔራዊ እግር ኳስ ሊግን እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድንን ያቀናጃል።

ምላሽ ይተው

Please enter your comment!
Please enter your name here