የካቲት 17 ቀን 2011 ዓ.ም በ9፡00 ሰዓት ዳንግላ ከተማ ከ ላስታ ላሊበላ የአንደኛውን ዙር የአንደኛ ሊግ እግር ኳስ ጨዋታ እየተካሄደ እያለ በ65ኛው ደቂቃ ኳስ ከጨዋታ ላይ እያለች በቀኝ ማዕዘን ወደ ግራ ማዕዘን በደቡብ ግብ በኩል የተመታ ኳስ ከጨዋታ ውጭ ለሆነ የዳንግላ ቡድን ቁጥር 23 ተጨዋች እንደደረሰች ረዳት ዳኛው ባንዲራውን በማንሳት ሲያመለክት በሦስት ሜትር ርቀት ከጀርባው የነበሩት የዳንግላ ቡድን ደጋፊዎች /ተመልካቾች/ በመረባረብ ባንዲራውን ወደ ላይ ሲያነሳ በመከልከል እንዲያወርድ ሲያደርጉት በዚያው ቅጽበት ኳስ ያገኘው የዳንግላ ቡድን ተጨዋች ኳስ እንዳገኝ በላስታ ላሊበላ ቡድን በረኛ በመጠለፋ ዋናው ዳኛ የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔ ሰጥተው ረዳት ኛውን ሲመለከቱ ረዳቱም ከዳንግላ ከተማ ቡድን ደጋፊዎች በመሸሸ ወደ ዋናው ዳኛ በመቅረብ የፍፁም ቅጣት ምት ከመስጠቱ በፊና ተጨዋቹ ላይ ተፈፀመ የተባለው ድርጊት ከመፈፀሙ በፊት ተጨዋቹ ከጨዋታ ውጭ የነበረ ስለመሆኑ ለማመልከት ባንዲራውን ወደ ላይ ሲያወጣ በተመልካቹ እንዳያወጣ በመደረጉ እንደሆነ ለዋናው ዳኛ ሲያሳውቅ ዳኛውም ፍፁም ቅጣትምቱን ሽሮ በመልስ ምት ጨዋታው እንዲጀመር በማዘዙ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተመልካች ወደ ጨዋታው ሜዳ በመግባት ረዳት ዳኛውን በእንጨት /በዱላ/ ጭንቅላቱን በመምታት እና መላ አካሉ ላይ በእጅ በመደብደብ እራሱን ስቶ እንደወደቀ፡፡

ዋናውን ዳኛን እንዲሁ ተመልካቾች እየተረባረቡ በመደብደብ የፊት አርቴፊሻል የሆነ አራት ጥርሱ በድብደባው ምክንያት እረግፈው እሱም እራሱን በመሳቱ በደጋፊው ማህበር አካላት እና በተጨዋቾች ሕይወታቸው ሊተርፍ እንደቻለ፡፡

በዕለቱ የቀይ መስቀል አምቡላንስና ሙያተኞች ባለመኖራቸው የዳንግላ ከተማ እግር ኳስ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ካሳሁን አስማረን እና በቦታው የነበሩትን የፖሊስ አዛዥ ዳኞች በጣም ስለተጐዱ እንዲታከሙ መኪና እንዲያቀርቡ እና ሕክምና እርዳታ ለማግኘት እንዲችሉ ከዚህ እንዲወጡ በተደጋጋሚ የዕለቱ ኮምሽነር ሲጠይቁ እነኝህ ዳኞችም ሆኑ አንተ ይህን ጨዋታ ካላጫወታችሁ የባስ ሕይወታችሁ ይጠፋል በማለት በማስፈራራትና ዛቻ ጭምር እየሰነዘሩ ባለበት ወደ ሜዳ የገባው ተመልካቹም የዕለቱን የጨዋታ አመራሮች በማስፈራራት ወደ ሜዳ በተጨማሪ ሌሎች ተመልካቾች ለመግባት በመጮህ ላይ እያሉ ስድቡ፣ ማስፈራራቱ በመቀጠሉ ከለላ የሚሰጣቸው ባለማግኘታቸው ለሕይወታቸው በመስጋት ጥርስ ረግፎ፤ ደም እየፈሰሳቸው ጨዋታው ከቁመበት ከ24 ደቂቃ በኃላ እነሱን እና እንግዳውን ቡድን ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጥቃት በመፍራትና ለመከላከል ሲሉ ሕጋዊ ባይሆንም ጨዋታው በፍፁም ቅጣት ምት እንዲጀመር እንዲያደርጉ በመገደዳቸው

የላስታ ላሊበላ ቡድንም እየተፈፀመ ባለው ድርጊት ባለማመኑ እንዲመታ ሲደረግ በረኛ ባለመገኘቱ የዕለቱን ጨዋታ በፊሽካ በመዝጋት ሁለቱም ቡድኖች እንዲወጡ እንዳደረጉ ከቀረቡት ሪፖርት ለመረዳት የተቻለ ሲሆን፣

 • ጨዋታው በፍፁም ቅጣት ምት እንዲጀመር ያደረጉት ሕጋዊ ሳይሆን ለሕይወታቸው ፈርተው በተመልካች ተገደው እንደሆነ፤
 • ይህን አስገድደው ካስፈፀሙአቸው በኃላ በአንቡላንስ ሄደው የሕክምና ርዳታ እንዲጋገኙ የተደረገ ስለመሆኑ፤
 • ማምሻውን ለሕይወታቸው በመፍራት በጭለማ ባሕርዳር እና እንጅባራ ተጉዘው ያደሩ ስለመሆኑ ከኮምሽነሩ ከዋናው ዳኛ እና 4ኛው ዳኛ ሪፖርት አቅረበዋል፡፡

ተመልካቾች ማሸነፍ እንዳለ ሁሉ መሸነፍ እንዲሚኖር አምኖ በመቀበል ደስታና እርካታ የሚገኘው ውድድሩ በሰላም ሲጠናቀቅ መሆኑን በመረዳት፤ ስሕተቶች ቢፈጠሩ እንኳን አጋጣሚ ሰለመሆኑ በመቁጠር የስፖርት መርህ ለሰላም፣ ለአንድነት፣ ለመግባባት፣ ለወንድማማችነት ለዘለቄታዊ ትብብርና ትስስር መሆኑን በማመን ለስፖርታዊ ጨዋነት መክበር የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

በዳንግላ ከተማ እግር ኳስ ሜዳ ላይ ግን በሀይል ውጤትን በማስለወጥ ዳኞችን በመደብደብ እና የስነ – ልቦና ተፅዕኖ በመፍጠር በዳኞች ላይ በተመልካች የደረሰው ጉዳት ሕክምና እንዲያገኙ ከማድረግ ይልቅ ሐይለቃል በመናገር ደማቸው እየፈሰሰ ጨዋታውን እንዲቀጥሉ ማስገደድ እና ለደረሰባቸው ጉዳት የሚመለከታቸው አካላት ሊከላከሉላቸው ያለመቻል፤ እንዲሁም እነሱም አባሪ ተባባሪ መሆን ፍፀም ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጭ የተፈፀመውን በማየትና በመመርመር በኢትዮጰያ እግር ኳስ ፌዳሬሽን ዲስኘሊን መመሪያ መሰረት በዳንግላ ከተማ እግር ኳስ ቡድን ላይ የሚከተለው የቅጣት ውሳኔ ተላልፏል፡፡

 1. የዳንግላ ከተማ እግር ኳስ ቡድን በሜዳው ውድድር እየተካሄደ ቡድኑ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ በመግባት በፈፀሙት የሀይል ጥቃት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲስኘሊን መመሪያ ክፍል 3 ምዕራፍ 3 በአንቀፅ 69 በንዑስ አንቀፅ 7 በፊደል ሀ መሰረት ባለሜዳው የዳንግላ ከተማ ቡድን በፎርፌ ተሸናፊ ሆኖ 0 ነጥብ እና 3 የግብ እዳ እንዲመዘገብለት በዕለቱ ጨዋታ ፎርፌ ያገኘው የላስታ ላሊበላ እግር ኳስ ቡድን 3 ነጥብ እና 3 ተጨማሪ ግብ እንዲመዘገብለት ተወስኗል፡፡
 2. የዳንግላ ከተማ እግር ኳስ ቡድን ተመልካች /ደጋፊ/ እረብሻ በመፍጠሩ ጨዋታው እንዲቋረጥ በማድረጉ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲስኘሊን መመሪያ ክፍል 3 ምዕራፍ 3 በአንቀፅ 69 በንዑስ አንቀጽ 8 በፊደል ተራ ሀ መሰረት ብር 150.000 /አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ/ የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል ተወስኗል፡፡

የቅጣት ገንዘቡን ይህ ውሳኔ ለክለቡ በደረሰው በ10 ቀናት ጊዜ ውስጥ ለፌዴሬሽኑ ሂሳብ ክፍል ገቢ እንዲያደርግ በተወሰነው ጊዜ ገደብ ካልከፈለ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲስኘሊን መመሪያ ክፍል 2 ምዕራፍ 3 በአንቀፅ 33 በፊደል ሸ መሰረት ክፍያው ለዘገየበት ቀኑ ካለፈበት ቀን ጀምሮ በየቀኑ ሁለት በመቶ መቀጮ ጨምሮ እንዲከፍል በተጨማሪ ከፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ምንም አይነት አገልግሎት እንዳያገኙ ተወስኗል፡፡

 1. በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲስኘሊን መመያ ክፍል 3 ምዕራፍ 3 በአንቀፅ 69 በንዑስ አንቀፅ 7/ሐ/ መሰረት ከዳንግላ ከተማ ከ200 ኪ.ሜ ያላነሰ 5/አምስት/ ጨዋታ ከሜዳው ወጥቶ በፌዴሬሽኑ በተመዘገበ ሜዳ እንዲጫወት ተወስኗል፡፡

ይህንንም በደንቡ መሰረት የማስፈፀም የአንደኛ ሊግ ኮሚቴ በመሆኑ እንደውሳኔው ለማስፈፀም እንዲችል ውሳኔው እንዲደርሰው ተወስኗል፡፡

 1. የዳንግላ ከተማ ቡድን ከሜዳው ውጭ እንዲጫወት በተወሰነው መሰረት ቅጣቱን ከመፈፀሙ በፊት ተመልካቾን ከጨዋታው ሜደ የሚለይ የሽቦ አጥር እንዲታጠር እንዲደረግ ይህ እስከሚፈፀም ከሜዳው ውጭ በገለልተኛ ሜዳ እየተጫወተ እንዲቆይ ተወስኗል፡፡
 2. በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲስኘሊን መመሪያ ክፍል 3 ምዕራፍ 3 በአንቀፅ 69 በንዑስ አንቀፅ 7/መ/ መሰረት የዳንግላ ከተማ እግር ኳስ ቡድን ካለው ወይም ወደፊት ከሚያገኘው 5/አምስት/ ነጥብ እንዲቀነስበት ተወስኗል፡፡
 3. የዕለቱን የጨዋታ አመራሮች ይህን ጨዋታ ጨርሳችሁ መውጣት አለባችሁ በማለት የደረሰባቸው ጉዳት ሕክምና እርዳታ እንዲያገኙ ማድረግ ሲገባ ሕክምና እንዳያገኙ በመከልከል ከሰበአዊነት ውጭ የሆነ ተግባር እንዳፈፀም ተባባሪ የነበሩት የእግር ኳስ ቡድን መሪ አቶ ካሳሁን አስማረ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲስኘሊን መመሪያ ክፍል 3 ምዕራፍ 3 በአንቀፅ 66 በንዑስ አንቀፅ 3 መሰረት ብር 25.000 /ሃያ አምስት ሺህ/ የገንዘብ ቅጣት እንደከፍል ተወስኗል፡፡

የቅጣት ገንዘቡን ይህ ውሳኔ ለክለቡ በደረሰው በ10 ቀናት ጊዜ ውስጥ ለፌዴሬሽኑ ሂሳብ ክፍል ገቢ እነዲያደርግ በተሰጠው ጊዜ ገደብ ገቢ ሳያደርግ ቀርቶ ቀኑ ካለፈበት ቀን ጀምሮ በኢትዮጰያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲስኘሊን መመሪያ ክፍል 3 ምዕራፍ 3 በአንቀፅ 65 በፊደል ሸ መሰረት በየቀኑ ሁለት በመቶ ታስቦ ተጨማሪ ቅጣት እነደከፍል በዚሁ ደንብ መሰረት ከፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ምንም አይነት አገልግሎት እንዳያገኝ ተወስኗል፡፡

 1. ጉዳት የደረሰባቸው ዋናው ዳኛ እና ረዳት ዳኛው ለሕክምና የሚያወጡትን ወጭ በሚያቀርቡት ማስረጃ መሰረት የዳንግላ ከተማ እግር ኳስ ቡድን እንዲከፍል ተወስኗል፡፡
 2. በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴርሽን ዲስኘሊን መመሪያ ክፍል 5 ምዕራፍ 2 በአንቀፅ 80 በንዑስ አንቀፅ 16 መሰረት በ30 ቀናት ጊዜ ውስጥ ለደጋፊዎች ስለ ስፖርታዊ ጨዋነትና የስፖርት ሕጐች ግንዛቤ እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ ሰርተው ለፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት በጽሑፍ ሪፖርት እንዲያቀርቡ ተወስኗል፡፡

 

አጋራ
Profile photo of የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል ነው። በ1943 እ.ኤ.አ. የተመሠረተ ሲሆን፣ በ1953 እ.ኤ.አ. የፊፋ፣ እንዲሁም በ1957 እ.ኤ.አ. የካፍ (CAF) አባል ሆነ። ይህ አካል የብሔራዊ እግር ኳስ ሊግን እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድንን ያቀናጃል።

ምላሽ ይተው

Please enter your comment!
Please enter your name here