የደደቢት እግር ኳስ ቡድን ከፋሲል ከተማ እግር ኳስ ቡድን በ26/08/2011 ዓ.ም በመቀሌ ስታዲየም ውድድር ያደረጉ ሲሆን በዕለቱ ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት የፋሲል ከነማ ተጫዋቾች በማሟሟቅ  ላይ እያሉ የመቀሌ ሰባ እንድርታ መሊያ የለበሱ ደጋፊዎች የትግራይ ክልላዊ መንግስት ባንዲራ እያውለበለቡ አፀያፊ ስድብ ይሰድቧቸው የነበረ መሆኑን፣ በ64ኛው ደቂቃ የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድን ጐል አግብቶ ጨዋታውን ለመጀመር መሀል ሜዳ ላይ እያሉ የመቀሌ ሰባ እንድርታ እግር ኳስ ቡድን ማሊያ የለበሱ ደጋፊዎች በፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድን ተጠባባቂ ተጫዋቾችና አሰልጣኞች ላይ የድንጋይ እሩምታ ያወረዱባቸው መሆኑን፣ የድንጋይ ውርወራውን በመሸሽ ተጫዋቾቹና አሰልጣኞቹ ወደሜዳ የገቡ መሆኑን የድንጋይ ውርወራው የቀጠለ መሆኑን ጨዋታው ለ1፡30 ደቂቃ የተቋረጠ መሆኑን፣ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ቤት ለማስገባት ሲሞከር ሦስት የፋሲል ተጫዋቾች በድንጋይ የተፈነከቱ መሆኑን፣ ከ1፡30 ሰዓት በኋላ ጨዋታው በዝግ ስታዲየም ተደርጐ ውድድሩ ሊጠናቀቅ የቻለ መሆኑ፣ በኘሪማች ስብሰባ ወቅት የደደቢትም ሆነ የፋሲል እግር ኳስ ቡድኖች ደጋፊ የለንም በማለት አሳውቀው የነበረ መሆኑ በዝርዝር ከጨዋታ አመራሮች ሪፖርት ቀርቧል፡፡ በሌላ በኩል የፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ በቁጥር ፋ/ከ/ስ/ክ/586/06፣ በ28/8/2011 ዓ.ም በተፅፈ አቤቱታ የመቀሌ 70 እንድርታ ደጋፊዎች ያደረሱበትን በደል በመግለፅ አቅርቧል፡፡

ስለዚህ የዲሲኘሊን ኮሚቴው በጨዋታ አመራሮች ሆነ በፋሲል ክለብ የቀረበውን ሪፖርትና አቤቱታ ከመረመረ በኋላ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

ከፍ ብሎ በጨዋታ አመራሮች ሆነ በፋሲል ከነማ ክለብ ተጫዋቾች እንዳቀረበው በፋሲል ከነማ ክለብ ላይ ችግር ሲፈጥሩ የነበሩት የመቀሌ 70 እንድርታ ክለብ ደጋፊዎች ናቸው በማለት ያቀረቡ ቢሆንም በዕለቱ የመቀሌ 70 እንድርታ ክለብ በሜዳው ላይ ውድድር ያልነበረው በመሆኑ በክለቡ ምክንያት ደጋፊ ረብሻ ረብሸዋል ማለት የማይቻል ሲሆን በሌላ በኩል ረብሸዋል የተባሉት የመቀሌ 70 እንድርታ ክለብ መለያ የለበሱ ስለመሆናቸው እንጂ የክለቡ ደጋፊዎች ስለመሆናቸውና የመቀሌ 70 እንድርታ ክለብ ፍላጐት ለማራመድ ስታዲየም ስለመግባታቸው የተረጋገጠበት ሁኔታ የለም፡፡

በቅድመ ውድድር ስብሰባ /በኘሪማች/ ወቅት የፋሲልም ሆነ የደደቢት ክለብ ደጋፊ የለንም በማለት አሳውቀው ከነበረ ወደ ሜዳ ለሚገባው ተመልካች ባለሜዳው ክለብ /ደደቢት/ኃላፊነት ለመውሰድ ዝግጁ አልነበረም ማለት ነው፡፡ ኃላፊነት የማይወስድ ከሆነ ደግሞ ሜዳው ለተመልካች ክፍት ማድረግ አይገባም ነበር፡፡

ነገር ግን ባለሜዳው ክለብ ደጋፊ የለንም ቢልም በውድድሩ ሜዳ ውስጥ ለሚፈጠረው የፀጥታ ችግር ኃላፊነት ያለበት ወይም ተመልካች ችግር ሲፈጥር መቆጣጠርና ችግር እንዳይፈጠር ማድረግ የነበረበት የደደቢት ስፖርት ክለብ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ የጨዋታ አመራሮች ያቀረቡት ሪፖርት እንደሚያረጋግጠው ባለሜዳው የደደቢት ስፖርት ክለብ ችግሩ በተፈጠረበት ወቅት ችግሩን ለማቆም ያደረገው ጥረት አነስተኛ ነው፡፡

በመሆኑም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሸን የዲሲኘሊን መመሪያ አንቀፅ 66/4/ሀ/ መሠረት፡-

  1. የደደቢት እግር ኳስ ስፖርት ክለብ ብር 150,000.00 /አንድ መቶ ሀምሳ ሺህ ብር/ እንዲቀጣ፤
  2. የደደቢት ስፖርት ክለብ በራሱ ሜዳ ላይ የሚያደርገውን ሁለት ጨዋታ በዝግ ስታዲየም ያለተመልካች እንዲጫወት ተወስኗል፡፡ ውድድሩ የሚካሄድበት ሁኔታና የውድድሩ ቀናት የሊግ ኮሚቴ እንዲወስን ተመርቶለታል፡፡
  3. የደደቢት ስፖርት ክለብ ደጋፊዎቹን የስፖርታዊ ጨዋነት በ30 ቀናት ውስጥ አስተምሮ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ሪፖርት እንዲያደርግ ተወስኗል፡፡
አጋራ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል ነው። በ1943 እ.ኤ.አ. የተመሠረተ ሲሆን፣ በ1953 እ.ኤ.አ. የፊፋ፣ እንዲሁም በ1957 እ.ኤ.አ. የካፍ (CAF) አባል ሆነ። ይህ አካል የብሔራዊ እግር ኳስ ሊግን እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድንን ያቀናጃል።

ምላሽ ይተው

Please enter your comment!
Please enter your name here