በአንደኛ ሊግ ተሳታፊ የሆነው የትግራይ ዋልታ ፖሊስ እግር ኳስ ክለብ ጨዋታውን ሐሙስ በ17/08/2011ዓ.ም ከ ደብረ ብርሃን ከነማ ጋር አድርጎ በ18/08/2011ዓ.ም በአፋር በኩል ወደ መቐለ ሲመለስ ከጠዋቱ 3፡30 ማንነታቸው ለጊዜው ባልታወቁ ታጣቂዎች በተከፈተ ድንገተኛ የጥይት ተኩስ አንድ የቡድኑ ተጫዋች ህይወት ሲያልፍ አምስት ተጫዋቾች ላይ የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ይታወቃል። ይህ ተግባር ፍጹም ሰብዓዊነት የጎደለው እና ይህ ተግባርን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አብዝቶ እንደሚያወግዘው አሁንም እንገልጻለን።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሀሙስ ሚያዚያ 24/08/2011ዓ.ም ድንገተኛ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ የተፈጠረው አሰቃቂ እና ሊወገዝ በሚገባው ተግባር ላይ ውይይት አድርጓል፤ በዚህ ውይይት በማናቸውም ነገሮች የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከትግራይ ዋልታ ፖሊስ ጎን እንደሚቆም የገለጸ ሲሆን ይህን ተግባር የፈጸሙት በአስቸኳይ ተጣርተው ለህግ እንዲቀርቡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት አቋማቸው መሆኑን በመግለጽ ፤ በተፈጠረው ጥቃት ህይወቱ ላለፈው ወጣት ቤተሰቦች እና የመቁሰል አደጋ ለደረሰባቸው ተጫዋቾች የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ባደረጉት ድንገተኛ አስቸኳይ ስብሰባ ውሳኔ አስተላልፈዋል። በጥቃቱ ህይወቱን ላጣው አማኑኤል ብርሃነ ቤተሰቦች የ50ሺህ ብር ድጋፍ እንዲሁም በጥቃቱ ለቆሰሉት ተጫዋቾች የ25ሺህ ብር ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያሳውቃል።

በጥቃቱ ህይወቱ ላለፈው አማኑኤል ብርሃነ ቤተሰቦች እና ወዳጅ ዘመዶች የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ አባላት መጽናናትን ይመኛሉ። የቆሰሉትም በቶሎ አገግመው ወደ ሚወዱት እግር ኳስ ይመለሱ ዘንድ ምኞታቸውን ገልጸዋል።

አጋራ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል ነው። በ1943 እ.ኤ.አ. የተመሠረተ ሲሆን፣ በ1953 እ.ኤ.አ. የፊፋ፣ እንዲሁም በ1957 እ.ኤ.አ. የካፍ (CAF) አባል ሆነ። ይህ አካል የብሔራዊ እግር ኳስ ሊግን እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድንን ያቀናጃል።

ምላሽ ይተው

Please enter your comment!
Please enter your name here