የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ይፋዊ የፊርማ ስነ-ስርአት ዛሬ ተከናወነ

አሰልጣኝ አሸናፊ ዋልያዎቹን ለቀጣዮቹ ሁለት አመታት ይመራሉ

አሰልጣኝ አሸናፊ ዋልያዎቹን ለቀጣዮቹ ሁለት አመታት የሚመሩ ሲሆን ብሄራዊ ቡድኑን ለ2019 የአፍሪካ ዋንጫ እና ለ2018 ቻን የማሳለፍ ግዴታ አለባቸው፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ አሰልጣኝ አሸናፊ ፣ የፌድሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ እና ዋና ፀሃፊው አቶ ወንዲምኩን አላዩ ተገኝተዋል፡፡

አሰልጣኝ አሸናፊ በብሄራዊ ቡድን ቆይታቸው ውጤት ማምጣት ካልቻሉ የውል ዘመኑን ሳይጠብቁ እንደሚለቁ እንዲሁም ከተሰራ በአፍሪካ ዋንጫው እስከሩብ ፍፃሜ መድረስ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ “ሁለት አመት ግዴታ አይደለም፡፡ ውጤታማ ካልሆንኩ መቆየት አልፈልግም፡፡ ይህ የእኔ አላማ ነው፡፡ ስመጣ ገንዘብ ለማግኘት አይደለም፡፡ ስመጣ ይህንን የተራብንበትን ቡድን ከእናንተ ጋር እና ከሙያ አጋሮቼ ጋር ተባብሬ ወደ ተሻለ ነገር ለማድረስ ነው፡፡ ይህንን በደንብ ልታሰምሩልኝ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አሁን የሚመረጡት ተጫዋቾች ወቅታዊ አቋማቸውን ያስመርጣቸዋል፡፡ ወቅታዊ አቋማቸውን ጥሩ የሆኑ የጨዋታ ልምድ ያላቸው ይፈለጋሉ፡፡ አሁን በመጣ ቁጥር ቡድን የሚፈርስ ከሆነ አስቸጋሪ ነው፡፡ ክፍተቶች ይኖራሉ በጋራ ከሰራን ጥሩ ነው፡፡ የምንገጥማቸው ቡድኖች በስም በተናጠል የምናያቸው ከሆነ ግን ልዩነታችን ሰፊ ነው፡፡ በታክሲ እና በእግር የመሄድ ያህል ነው፡፡ ነገር ግን ህብረት ካለን አንድነት ካለን ይቻላል፡፡ ለሩብ ፍፃሜ ታልፋለህ ተብዬ ተጠይቄያለው፡፡ አደርገዋለው ብዬ አስቤ ነው፡፡ መናገር እና መስራት ይለያያሉ፡፡ ግን ጠንክሮ ከተሰራ የማይቻል ነገር የለም የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡”

አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ በበኩላቸው ፌድሬሽኑ አሁንም ፊቱን ወደ ሃገር ውስጥ አሰልጣኝ ያዞረው ከውጪ አሰልጣኞች በንፅፅር በውጤት ደረጃ የተሻሉ ስለሆኑ ነው ብለዋል፡፡ “ቴክኒክ ኮሚቴው የውጭ አሰልጣኝ እና የሃገር ውስጥ አሰልጣኝ በብዙ አንፃር ነው የታየው፡፡ ቴክኒክ ኮሚቴው ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ሁለት ስብሰባዎች አድርጓል፡፡ በብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ደረጃ እኛም የቀጠርነውን የውጭ አሰልጣኝ እንዲሁም ከእኛ በፊት የነበሩትን አሰልጣኞች በደንብ ነው የገመገምነው፡፡ ኢትዮጵያዊያኖች እና የውጭ አሰልጣኞች ያመጡትን ውጤት በደንብ አይተናል፡፡ ለአንድ የውጭ አሰልጣኝ የሚከፈለውንም ወጪ በእዚው ላይ አጠቃለናል፡፡ ስናይ ያለው ጠቀሜታ ትንሽ ነው፡፡ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ያለው ግዜ አጭር በመሆኑ ፊታችንን ወደ ሃገር ውስጥ አሰልጣኝ አዙረናል፡፡”

 

አሰልጣኝ አሸናፊ በበኩላቸው በቅርብ ግዜ የአሰልጣኝ ቡድናቸውን ይፋ እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል፡፡ “ስራዬን በቀላሉ ለማከናወን እንዲያስችለኝ ይረዱኛል ብዬ ያሰብኳቸው በማሰልጠን ሙያ ላይ ያሉ ወደ 3 አሰልጣኞች፣ ድጋፍ ሰጪ የስነ ልቦና ባለሙያ፣ የስነ ምግብ ባለሙያ፣ የአካል ብቃት ባለሙያ ወዘተ አካተናል፡፡ ምክትል አሰልጣኞቹን በተመለከተ ለመመልመል የታሰበው ተጫውተው ያለፉ በክለብ ደረጃ ቢቻል ብሄራዊ ቡድን እንዲሁም የሃገራችንን ሊግ በቅርበት የሚያውቁ፣ ለአምስት አመታት ያህል በስራው የቆዩ የስፖርት ሳይንስ ምሩቃን አሰልጣኞችን ለማካተት ተሞክሯል፡፡”

አሰልጣኙ የአቋም መለኪያ ሶስት ጨዋታዎችን በግንቦት ወር ለማካሄድ እንዳቀዱ እና እቅዱ እንዲሰምር ፌድሬሽኑ ከወዲሁ ስራ መጀመሩን አቶ ዘሪሁን ተናግረዋል፡፡ ከዩጋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ከካሜሮን ወይም ናይጄሪያ ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን ለማካሄድ በእቅድ ተይዟል፡፡ አሰልጣኝ አሸናፊ በመጀመሪያ የብሄራዊ ቡድን ስብስባቸው ልምድ ያላቸውን እና ታዳጊዎችን ለማካተት አስበዋል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ከዋሊያዎቹ የራቁ ተጫዋቾችንም የማግባባት ስራ እንደሚሰሩ አሰልጣኙ ጨምረው ጠቅሰዋል፡፡ አቅም ያላቸውን ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾችን ወደ ቡድናቸው ለማካተት በራቸው ክፍት መሆኑን እንዲሁም በስራው ላይ ሚዲያውን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

አጋራ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል ነው። በ1943 እ.ኤ.አ. የተመሠረተ ሲሆን፣ በ1953 እ.ኤ.አ. የፊፋ፣ እንዲሁም በ1957 እ.ኤ.አ. የካፍ (CAF) አባል ሆነ። ይህ አካል የብሔራዊ እግር ኳስ ሊግን እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድንን ያቀናጃል።

ምላሽ ይተው

Please enter your comment!
Please enter your name here