አዲስ አበባ የካቲት 26/2011ዓ.ም፤የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ያዘጋጁት የምክክር መድረክ የካቲት 23/2011ዓ.ም በብሉ ስካይ ሆቴል ተካሄደ፡፡ በዚህ የውይይት መድረክ አንጋፋ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች እና በአሁን ሰዓት በፕሪሚየር ሊጉ የተለያዩ የወንድ እና የሴት ክለቦችን በማሰልጠን ላይ የሚገኙ አሰልጣኞች ፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ አባል እና የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው እንዲሁም የብሄራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ተሳትፈውበታል፡፡
ውይይቱ የተጀመረው ለኢትዮጵያ እግር ኳስ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያደረጉ በህይወት የሌሉ ባለውለተኞችን በህሊና ጸሎት በማሰብ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር በጋራ መስራት አለብን የብሄራዊ ቡድናችን ጉዳይ ለሁላችንም ጉዳይ ሊሆን ይገባል እርስ በእረስ ያለው መገፋፋት ታሪክ ሆኖ መቅረት አለበት የእግር ኳሳችን ውድቀት የእያንዳደንዱ አሰልጣኝ ውድቀት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ያሉ ሲሆን የብሄራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ሁሉም አሰልጣኝ ለሀገር የሚጠቅም ስራ መስራት አለበት መሸዋወዱ ይበቃል ለሆዳችን ሳይሆን ለሀገር ለትውልድ የሚጠቅም ስራ ሰርተን ማለፍ አለብን የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ለውይይት እንዲያግዝ ሁለት መነሻ ጽሁፎች እና አንድ ጥናታዊ ጽሀፍ ቀረቧል፡፡ በኢንስትራክተር መኮንን ኩሩ የቀረበው መነሻ ጽሁፍ 21 ነጥቦች የተካተቱበት የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ልማት በምን መልኩ መጓዝ እንዳለበት የሚያሳይ ታዳጊዎች ላይ ምን መደረግ እንዳለበት ከእያንዳንዱ ባለድርሻ አካል ሚጠበቀውን የዳሰሰ መነሻ ጽሁፍ ነው፡፡

በፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ በነበሩ የእግር ኳስ ክለቦች ውስጥ የሚጫወቱ እግር ኳስ ተጫዋቾች ከየትኛው አካባቢ የተገኙ ናቸው የሚል ጥናት በ2005ዓ.ም ተደርጎ የነበረ ሲሆን የዚህ የጥናት ግኝት ለተሳታፊዎች የጥናቱ ባለቤት በሆኑት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የስፖርት ሰነ ልቦና ባለሙያ ሳሙኤል ስለሺ አማካኝነት ቀርቦ አብዛኛው በወቅቱ ይጫወቱ የነበሩት መነሻቸው ከከተሞች እነደነበረ እንዲሁም በወቅቱ ተጫዋቾችን ረዘም ያለ ጊዜ አለማስፈረም ችግር ውስጥ የከተታቸው እና ረጅም ጊዜ አብረው የቆዩ ተጫዋቾች ለቡድን ስኬት ምን ያህል እንዳገዙ በጥናቱ ግኝት ላይ በደንብ ተብራርቷል፡፡

ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ያቀረቡት የውይይት መነሻ ሀሳብ ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን ለመስራት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ከአለማቀፍ የእግር ኳስ ማህበር ጥናት ጋር በማያያዝ አቅርበዋል፡፡ የተጫዋቾች ጥራት ደረጃ፤ የአሰልጣኖች ና የስልጠና ደረጃ፤ የክለቦች የጥራት ደረጃ ፤ የኢንተርናሽናል ተጫዋቾች መገኘት፤ የብሄራዊ ቡድን አስተዳደር የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮችን በጥልቀት በማንሳት አብራርተዋል፡፡ እነዚህ ርእሶች የተሻለ ብሄራዊ ቡድን ለመስራት ወሳኞች ናቸው፡፡ ብሄራዊ ቡድን ጥንካሬው እና ድክመቱ የክለቦቻችን የስራ ውጤት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በውይይቱ የታደሙት አሰልጣኞች እርስ በእርስ ያለው መከባበር እና ልምድ ለመለዋወጥ ያለው ዝግጁነት አነስተኛ መሆን፤ የብሄራዊ ቡድንን አሰልጣኝ ለማገዝ ቀና አለመሆን ፤ የክለብ አመራሮች ለአሰልጣኞች ረዘም ያለ ኮንትራት አለማቅረብ ለሀገር የሚጠቅም ስራ አሰልጣኞች እንዳይሰሩ አድረጓል፤ ለአሰልጣኞች ደረጃ አለመውጣቱ ማን በየትኛው ደረጃ ማሰልጠን እንዳለበት የሚገልጽ ስርዓት አለመዘርጋቱ በኢትዮጵያ እግር ኳስ አሰለጣጠን ላይ ክፍተት ፈጥሯል፡፡


እንዲሁም ሙያዊ የምክክር መድረኮች አለመኖር የእውቀት ሽግግር እንዳይኖር አድርጓል፤ አስልጣኞች እውቀታቸውን ሊያዳብሩ የሚችሉበት ማዕከል አለመኖር እንዲሁም የሚሰጡ ስልጠናዎች በደንብ የሚመዝኑ አለመሆናቸው ስልጠናው ላይ የተሳተፈ ሁሉ ሰርትፍኬ የሚያገኝበት መሆኑ እንደ ችግር ተነስቷል፡፡
ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች መካካል ያለው መከባበር አንዳንድ ክለቦች ላይ ተጫዋቾች ከአሰልጣኙ በላይ የሚሰሙበት ፤ ተጫዋቾች ራሳቸው የሚሰሩትን ልምምድ የሚመርጡበት በአሰላለፍ ጣልቃ የሚገቡበት፤ በአሰልጣኞች ቅጥር እጃቸው የሚረዝም ተጫዋቾች አሉ ይህ ደግሞ በአሰልጣኞች እና በተጫዋቾች መካከል ያለው መከባበር እንዲቀንስ ሆኗል የሚሉ ሀሳቦች ተነስተዋል፡፡
ግብ ጠባቂ ላይ ሰፊ ክፍተት አለ የህግ ማዕቀፍ ቢወጣለት ጥሩ ነው፤ አመራረጣችን በራሱ ችግር አለበት፡፡ ጠንካራ ክለብ ከሌለ ጠንካራ ብሔራዊ ሊኖር አይችልም ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ መወጣት እንዳለበት ከተሳታፊዎች አጽኖት የተሰጠው ጉዳይ ነው፡፡
ከአሰልጣኞች ስልጠና ጋር በተያያዘ ወደፊት የአሰልጣኞች ስልጠና ከተወሰደ በኋላ ስልጠናውን ሲወስዱ ያስመዘገቡት ውጤት እንዲታወቅ እንዲሁም ማሰልጠን የሚገባቸው ደረጃ በየትኛው ውድድር ላይ ተሳታፊ ሚሆኑ ክለቦች እንደሚሆኑ በግልጽ ይጠቀሳል ተብሏል፡፡
በስተመጨረሻም በውይይቱ የተነሱት ነጥቦች በሙሉ በሰነድ መልክ ተዘጋጅተው በቀጣይ ውይይት እንዲቀረቡ ይደረጋል ተብሏል፡፡

አጋራ
Profile photo of የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል ነው። በ1943 እ.ኤ.አ. የተመሠረተ ሲሆን፣ በ1953 እ.ኤ.አ. የፊፋ፣ እንዲሁም በ1957 እ.ኤ.አ. የካፍ (CAF) አባል ሆነ። ይህ አካል የብሔራዊ እግር ኳስ ሊግን እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድንን ያቀናጃል።

ምላሽ ይተው

Please enter your comment!
Please enter your name here