ኢትዮጵያ በየካቲት እና በመጋቢት ወራት የአለም አቀፍ እግር ኳስ ማህበራት (ፊፋ) አለም አቀፍ ስብሰባና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ጠቅላላ ጉባኤ ታስተናግዳለች፡፡
በዓለም አቀፍ እግር ኳስ ስፖርት ማህበር /ፊፋ/ በተዘጋጀውና እ.አ.አ ከፌብሩዋሪ 20–23/2017 በሚካሄደው የፊፋ አለም አቀፍ የሥራ አስፈፃሚዎች ስብሰባ 100 የሚደርሱ ከ20 ሃገሮች የተወጣጡ የእግር ኳስ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የፊፋ ባለሥልጣኖች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡ እንግሊዝኛ ተናጋሪ የአውሮፖ የእስያ እና የአፍሪካ ሀገሮች ተካፋይ በሚሆኑበት የእግር ኳስ ልማት ስብሰባ ላይ የፖኪስታን፣ የኦማን፣ የሳኡዲ አረቢያ፣የቦትስዋና፣ የቻድ፣ የኢትዮጵያ፣ የጋምቢያ፣ የሌሴቶ፣ የማላዊ፣ የደቡብ ሱዳን፣ የስዋዚላንድ፣ የዛምቢያ፣ የዙምባብዌ፣ የሰሜን አየርላንድ ሪፖብሊክ፣ የስሎቬኒያ፣ የስዊዲን፣ የቱርክና፣ የዌልስ እግር ኳስ ማህበራት ፕሬዝዳንቶችና ዋና ፀሐፊዎች ተካፋይ ይሆናሉ፡፡
በስብሰባው ፊፋ በፕሬዝዳንቱና ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ልማትን በሚመሩ የካውንስል አባላቱ እንደሚወከል ታወቋል፡፡ ለስብሰባው ቅድመ ሁኔታ ለማመቻቸትም የፊፋ የውድድር ስራዎች ማኔጀር ሳጋንታ አንቶኔንታ ዛሬ እኩለ ቀን ላይ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
በተመሳሳይ 39ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ እ.አ.አ ከማርች 16–17/2017 በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ይካሄዳል፡፡ በጉባኤው የሁሉም የካፍ አባል ሀገሮች ተወካዮችን ጨምሮ ከ380 በላይ እንግዶች ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የፊፋ የሥራ አስፈፃሚ ሰብሳባና የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄዱን መነሻ በማድረግ አንዳንድ መገናኛ ብዙሀን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የካፍ ዋና ጽህፈት ቤት ከካይሮ ወደ አዲስ አበባ እንዲዛወር ፍላጐት እንዳለው በመግለፅ ያስተላለፉት ዘገባ መሰረት ቢስ መሆኑን ፌዴሬሽኑ በእዚህ አጋጣሚ ያስገነዝባል፡፡ኢትዮጵያ በዓለምና በአህጉራዊ መዳረሻነቷ እንዲሁም በኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አድማስና ቀልጣፋ አገልግሎት ምክንያት የፊፋ ማዕከል እንድትሆን መታጨቷን ተከትሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለፊፋ ጽህፈት ቤት አገልግሎት የሚውል ህንፃ ለማግኘት ጉዳዩ ለሚመለከተው መንግስታዊ አካል ጥያቄ አቅርቦ ምላሹን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡

አጋራ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል ነው። በ1943 እ.ኤ.አ. የተመሠረተ ሲሆን፣ በ1953 እ.ኤ.አ. የፊፋ፣ እንዲሁም በ1957 እ.ኤ.አ. የካፍ (CAF) አባል ሆነ። ይህ አካል የብሔራዊ እግር ኳስ ሊግን እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድንን ያቀናጃል።

ምላሽ ይተው

Please enter your comment!
Please enter your name here