ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ተገቢነት የሌለው ደብዳቤ በመፃፋ በ21/06/2011 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲስኘሊን ኮሚቴ የቅጣት ውሳኔ አስተላለፈ፡፡

በአጀንዳው ላይ ተገቢውን ውሳኔ ለመስጠት እንዲቻል ኮሚቴው የነገሩን አመጣጥ በዝርዝር ተመልክቷል፡፡

 1. ይኸውም የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በ15/04/2011 ዓ.ም ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በፃፈው ደብዳቤ “ስለ አልቢትር ኮሚቴ ይመለከታል” የሚል ርዕስ በመስጠት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሚገኙት ዋና ዋና ቋሚ ኮሚቴዎች ውስጥ አንዱ የአልቢትር ኮሚቴ መሆኑን፣ አባላቱም በስፖርቱ ቤተሰብ ዘንድ በገለልተኛነታቸውና በመልካም ስብእናቸው የታወቁና ዕምነት ሊጣልባቸው የሚገባ መሆኑ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ሙያ በሌላቸውና ገለልተኛነት በሌላቸው በመመራት ላይ በመሆኑ ከፍተኛ አድሎ እየሰሩ ጠብና ረብሻ እንደሚነሳ ከፍተኛ ስጋት አለን፣ ችግሩ ከመባባሱ በፊት የአልቢትር ኮሚቴው በሙያተኛና በገለልተኛ አካላት ይዋቀር፣ በክለባችን ላይ የደረሰው በደል ሰብሳቢው ገለልተኛ ባለመሆናቸው ጉዳቱን በየጊዜው በመቀበል ላይ የምንገኝ መሆኑን፣ ገለልተኛና ሙያተኛ ባልጠፋበት ሃገር የክለብ ተልእኰን የሚያስፈፅሙ ሰዎችን መድቦ ወደፊት ሰፖርቱ ለከፋ አደጋ ማዘጋጀት ተገቢ እንዳልሆነ በመግለፅ ምላሽ እንዲሰጠን ጠይቀን ምላሽ አልተሰጠንም፣ በአሁኑ ጊዜ የክለቦች ውጤት በሜዳ ላይ ሳይሆን በቢሮ ውስጥ እየተሰራ ነው፡፡

ማራኪ ጨዋታ በማሳየት የምንሰበሰበውን ከ40 ሚሊዮን ብር ያላነሰ ዓመታዊ ገንዘብ በተራ ተንኰልና ደባ ሜዳ ላይ አፍሰን ለመግባት ህሊናችን አይፈቅድም፡፡ በመሆኑም የአልቢተር ኮሚቴ ሰብሳቢ ተብለው የተሰየሙት ሙያዊ እውቀት የሌላቸው፣ ውድድሩን በገለልተኛነት ሊመሩ የማይችሉና ለስፖርቱ ያላቸውን ዝቅተኛ ግምት ቀደም ሲል ሀገራችን በማስቀጣት ሪከርድ አላቸው፣ ውድድሩን በሜዳ ውጤት ሳይሆን በቢሮ ዋንጫ ምደባ ከመደረጉ በፊት አስቸኳይ መፍትሄ ይሠጠን፣ ይህ ካልሆነ ክለባችን አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል በማለት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፅፏል፡፡

 1. የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከፍ ብሎ የተጠቀሰውን በኢትዮጵየ ቡና ስፖርት ክለብ የተፃፈውን ከተመለከተ በኃላ በ21/05/2011 ዓ.ም ፅፎ ለዲስኘሊን ኮሚቴ ባቀረበው ክስ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የፌዴሬሽኑ ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴን አስመልክቶ ተገቢ ያልሆነ አስተያየት የፃፈ በመሆኑ ይህንኑ ለማጣራትና ለማስተካከል እንዲቻል በቁጥር ኢ/እ/ኳ/ፌ 0244 ፣ በ18/04/2011 በተፃፈ ደብዳቤ ተፈፀመ የተባለው ችግር በተመለከተ ማስረጃ እንዲያቀርብ ተጠይቆ ከአንድ ወር በላይ ቢጠበቅም ያላቀረበ በመሆኑ የዲስኘሊን ኮሚቴ በፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብና በዲስኘሊን መመሪያ መሠረት አስፈላጊውን ውሳኔ እንዲሰጥበት በማለት 3 ገፅ ማስረጃ አያይዞ አቅርቧል፡፡
 2. የዲስኘሊን ኮሚቴው ከላይ የተገለፁትን ከተመለከተ በኃላ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለዲስኘሊን ኮሚቴ ባቀረባቸው የክስ አቤቱታ ላይ ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ ወይም የመከላከያ መልስ እንዲያቀርብ በቁጥር ኢ/እ/ፌ/ አ-9/016 በ30/05/2011 ዓ.ም ተፅፎለት ክለቡም በቁጥር ኢ/ስ/ክ/ሰአ-1185/11 በ07/06/2011 ዓ.ም ምላሽ ሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በሰጠው ምላሽም የደረሰብን በደልና የዳኛ አመዳደብ ችግር ገልፀን ፌዴሬሽኑ ጉዳዩን አጢኖ ማስተካከያ እንዲያደርግ ጠይቀን እያለ በሰዎች ሰሜትና ፍላጐ የሚካሄድ ጉዳይ ማስረጃ አቅርቡ ማለት የክለቡን ስሜት በእጅጉ የሚጐዳ ነው በዳኝነት አካሉና በዳኝነት ኮሚቴ ሰብሳቢ ላይ ጥርጣሬ አለን ወይም እምነት የለንም የሚለው ምላሻችን መልሱን የሚሰጥ መሆኑን እንተማመናለን በማለት በማስረጃ ሳያስደግፍ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

 1. የዲስኘሊን ኮሚቴው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቀረበውንም ሆነ በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የተሰጠውን መልስ በጥልቀት መርምሯል፡፡
  • የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በ15/04/2011 ዓ.ም ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንደፃፈው በክለቡ ላይ የዳኞች በደል ደርሶበት ከሆነ ወይም በ7/06/2011 ዓ.ም ምላሽ እንዳቀረበው በዳኝነት አካሉ ላይ ወይም በሰብሳቢው ላይ ጥርጣሬ አለኝ ካለ ጥርጣሬውን በማስረጃ አስደግፎ በችግሩ ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ለፌዴሬሽኑ ማቅረቡ ችግር ያለው አይደለም፡፡ ነገር ግን ከላይ በተራ ቁጥር 1 ላይ እንደተዘረዘረው የዳኝነት ምደባ ላይ ችግር ስለመኖሩ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የገለፀበት ሁኔታ በአብዛኛው በግለስብ ላይ ያተኰረ እንጂ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የዳኞች ኮሚቴን ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ የኢትዮጰየ ቡና ስፖርት ክለብ ያቀረበው የዳኞች ኮሚቴ የሚመራው ሙያ በሌላቸውና ገለልተኛ ባልሆኑ ከፍተኛ አድሎ የሚሠሩ መሆኑን በተለይም ሰብሳቢው ገለልተኛ ያልሆኑ፣ የክለብ ተልዕኰን የሚያስፈፅሙ የክለቦች ውጤት በሜዳ ላይ ሳይሆን በቢሮ ውስጥ መሆኑን የአልቢትር ኮሚቴ ተብለው የተሰየሙት ሙያዊ እውቀት የሌላቸውና ውድድርን በገለልተኝነት ሊመሩ የማይችሉ ናቸው የሚል ነው፡፡

እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በዳኞች ኮሚቴና በሰብሳቢው ላይ ስላቀረበው ጉዳይ ምላሽ እንዲሰጥ በዲስኘሊን ኮሚቴ በተጠየቀ ጊዜ የጠቀሳቸው ችግሮች ስለመኖራቸው በማስረጃ አስደግፎ ማቅረብ የሚገባው ሆኖ እያለ ማስረጃ አቅርቡ መባላችን ክለባችንን የሚጐዳ ነው፣ በዳኞች ኮሚቴም ሆነ በሰብሳቢው ላይ እምነት የለንም ብለን የሰጠነው በቂ መልስ ነው ከማለት ውጪ የዳኞች ኮሚቴም ሆነ የሰብሳቢው ጥፋት ናቸው በማለት ሰላቀረቧቸው ጉዳዩች በምንም ሁኔታ ወይም ማስረጃ አላስረዳም፡፡

 • የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴም ሆነ በሰብሳቢው በኩል ተፈፅሟል ያላቸውን ድርጊቶች በማስረጃ ካላረጋገጠ ደግሞ ክለቡ በብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴም ሆነ በሰብሳቢው ላይ የስም ማጥፋት ድርጊት መፈፀሙን ድምዳሜ ላይ የሚያደርስ ነው፡፡

ይኸውም የበሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ የተዋቀረውና የሚመራው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ለስራ አስፈፃሚ አባልነት በተመረጡት ግለሰብ ሰብሳቢነትና በሃገሪቷ ውስጥ በእግር ኳስ ዳኝነት ኢንተርናሽናል ደረጃ በደረሱ አባላት በመሆኑ ብቃት የሌላቸው ስለመሆኑ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የጠቀሳቸው ጥፋቶች መቅረብ ያለበት በማስረጃ ተደግፎ ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡

 1. ስለዚህ የዲስኘሊን ኮሚቴ ጉዳዩን ከመረመረ በኃላ የሚከተለው ውሳኔ አሳልፏል፡-
  • የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በተቋም ደረጃ የፌዴሬሽኑ አመራሮችን ስምና ዝና ያጐደፈ  በመሆኑ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የዲስኘሊን መመሪያ ምዕራፍ 3 ክፍል 3 አንቀፅ 66/2/ለ/ መሠረት ብር 50.000.00 /አምሳ ሺህ ብር/ እንዲቀጣ ተወስኗል፡፡
  • የተወሰነውን የቅጣት ገንዘብ ውሳኔው በደረሳቸው በ10 ቀናት ውስጥ እንዲከፍሉ በተባለው ጊዜ ካልከፈሉ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲስኘሊን መመሪያ ክፍል 2 ምዕራፍ 5 በአንቀፅ 33 በፊደል ሸ እና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲስኘሊን መመሪያ ክፍል 5 ምዕራፍ 2 በአንቀፅ 80 በፊደል ሀ በተራ ቁጥር 5 መሰረት የፍትህ አካሉ በወሰኑት ጊዜ ገደብ ተግባራዊ የማድረግ እና መክፈል ግዴታ አለበት በተወሰነው ጊዜ ገደቡ ገቢ የማደረግ እና ካልከፈለ ደግሞ ክፍያው ለዘገየበት በየቀኑ ሁለት በመቶ መቀጮ ጨምሮ ኢንዲከፍል፣ በተጨማሪ ከፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ምንም አይነት አገልግሎት እንዳያገኙ ተወስኗል፡፡
አጋራ
Profile photo of የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል ነው። በ1943 እ.ኤ.አ. የተመሠረተ ሲሆን፣ በ1953 እ.ኤ.አ. የፊፋ፣ እንዲሁም በ1957 እ.ኤ.አ. የካፍ (CAF) አባል ሆነ። ይህ አካል የብሔራዊ እግር ኳስ ሊግን እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድንን ያቀናጃል።

ምላሽ ይተው

Please enter your comment!
Please enter your name here