የቻን 2020 ውድድር አዘጋጅ የሆነችው ኢትዮጵያ የስታዲየሞች ዝግጅች ምን ይመስላል የሚለውን ለመመልከት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) 3 አባላት ያሉት መዛኝ ቡድን በመላክ ከዓርብ 29/6/2011 እስከ ሰኞ 02/07/2011 ዓ.ም ድረስ ውድድሩ በሚካሄድባቸው 4 ከተሞች የሚገኙ ስታዲየሞችን እና መለማመጃ ሜዳዎችን ጐብኝቷል፡፡

በጉብኝቱ የኡጋንዳ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኘሬዚዳንት እና የካፍ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሞስስ ማጐጐ ፣ የካፍ ሥራ አስፈፃሚ አባል የታንዛኒያው ሊዮዴጋር ቴንጋ እና የካፍ የክለብ ላየሰንሲግ ማኔጀር ግብፃዊው አህመድ ሀራዝ የገምጋሚ ቡድኑ አባላት እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኘሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ክለብ ላይሰንሲግ ማኔጀር አቶ ተድላ ዳኛቸው እና ከኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ኢንጂነር አስመራ ግዛው እንዲሁም ሁለት የፎቶ ግራፍ ባለሙያዎች የጉብኝቱ አካል ነበሩ፡፡ ጉብኝቱ በሀዋሳ፣ መቐሌ፣ ባህርዳር እና በአዲስ አበባ በቅደም ተከተል ተካሂዷል፡፡

የሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም

በሀዋሣ ዓለም አቀፍ ስታዲየም በነበረው ጉብኝት የክልሉ የስፖርት ኮሚሽን አመራሮች በተገኙበት ጉብኝቱ ተካሂዷል፡፡ በአንደኛው ጉብኝት እንዲስተካከሉ የተባሉት ምን ያህል ተሻሽለዋል የሚለውን ጥያቄ ጨምሮ በስታዲየሙ የሚገኙ ክፍሎችን ማለትም መልበሻ ክፍል ፣ የዳኞች ክፍል ፣ የአሰልጣኞች ቢሮ፣ የኳስ አቀባዮች ክፍል፣ በካፍ ውድድሩን ለመምራት የሚመጡ አካላት ቢሮ፤ እንዲሁም በሜዳው ላይ ያለው ሣር ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ የሚል አስተያየት በተሰጠው መሠረት ምን ደረጃ እንዳለ ተመልክተዋል፡፡ ሙሉ በሙሉ ሣር ተነስቶ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ፤ በማታ ጨዋታዎችን ማካሄድ እንደሚቻል የካፍ ገምጋሚ ኮሚቴ ተገንዝቧል፡፡ በስታዲየም የተመልካቾች እና የክብር እንግዶች መቀመጫ አለመኖሩን ታዝበዋል፡፡

በተጨማሪም አራት መለማመጃ ሜዳዎችን ተምልክተዋል፤ እነዚህም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም፤የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የእርሻ ኮሌጅ እግር ኳስ ሜዳ፤ የሐዋሳ ሰውሰራሽ ሳር የተነጠፈበት ስታዲየም እና በሐዋሳ አለም አቀፍ ስታዲየም ዙሪያ የሚገኘው መለማመጃ ሜዳን ጎብኝተዋል፡፡ እያንዳንዱ ሜዳ መልበሻ ክፍሎች ፤ የገላ መታጠቢያ ቤቶች እና የመጸዳጃ ቤቶች መሟላት አለመሟላታቸውን በግምገማቸው ተምልክተዋል፡፡

የትግራይ ዓለም አቀፍ ስታዲየም

 

ይህ የካፍ ገምጋሚ ቡድን የሁለተኛ ቀን ውሎውን ወደ መቐለ በመሄድ የትግራይ ዓለም አቀፍ ስታዲየምን ጐብኝተዋል፣፣ በትግራይ ዓለም አቀፍ ስታዲየም በቂ የሚባሉ ለውድድሩ አስፈላጊ የሆኑ ክፍሎች ቢኖሩም ገና ያልተጠናቀቁ መሆኑን ጐብኝው ቡድን ባደረገው ምልከታ አስተውሏል፡፡ በስታዲየሙ የማታ ጨዋታዎች ለማድረግ የባውዛ መትከል ሥራ አለመሠራቱን በመልከታቸው አይተዋል፡፡ በስታዲየም ውስጥ ስክሪን አለመገጠሙን፣ የተመልካች የVIP ወንበሮች አለመኖራቸውን የስታዲየሙ ሥራ ሙሉ በሙሉ አልተጠናቀቀም በሚል ደረጃ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ሁለቱን የዩኒቨርሲቲው ሜዳዎች እና በትግራይ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ዙሪያ የሚገኙትን መለማመጃ ሜዳዎች ቡድኑ ተመልክቷል፡፡

የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም

የሦስተኛ ቀን ምልከታ የተካሄደበት ስታዲየም ሲሆን ከሌሎች ስታዲየሞች በውስጡ የያዘው ክፍሎች አብዛኛው የተጠናቀቀ እና ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን ተመልክተዋል፤ ነገር ግን እነዚህ ክፍሎች በውስጣቸው ማካተት የሚገባቸው ቁሳቁሶች የማሟላት ሥራ ይቀራቸዋል፡፡ እንዲሁም ተጨማሪ ሁለት ቡድኖችን ማስተናገድ ያለባቸው መልበሻ ክፍሎች መሠራት እንዳለባቸው ፤ የVIP ቦታ በደንብ መሠራት እንዳለበት በጉብኝቱ ወቅት ተነግሯል፡፡ እንዲሁም የማታ ጨዋታዎችን ለማድረግ የባውዛ መብራቶች አለመኖራቸውን፣ ትልቅ ስክሪን በስታዲየም አለመኖሩን መታዘብ ችለዋል፤ የVIP ወንበሮች እንደሚያስፈልጉ በጉብኝታቸው ወቅት አበክረው ገልጸዋል ፡፡ በምልካም ጎኑ ከታዩ ጉዳዮች መካከል ትልቅ የመብራት ጄኔሬተር መገጠሙን አድንቀዋል፡፡

በስታዲየሙ ዙሪያ ያሉ ሁለት የመለማመጃ ሜዳዎችን፤ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲን የስፖርት አካዳሚ ሜዳ እና የአጼ ቴዎድሮስ ስታዲየምን ጎብኝተዋል፡፡ እያንዳንዱ ሜዳ መልበሻ ክፍሎች ፤ የገላ መታጠቢያ ቤቶች እና የመጸዳጃ ቤቶች በቶሎ መሟላት እንዳለባቸው ገምጋሚው ቡድን አሳውቋል ፡፡

የአደይ አበባ ስታዲየም

የካፍ የስታዲየሞች ገምጋሚ ኮሚቴ በ4ኛ ቀን ውሎው በአዲስ አበባ የአደይ አበባ ስታዲየምን ገብኝቷል፡፡ የስትራክቸር ሥራው ሙሉ በሙሉ ስታንዳርዱን በሚያሟላ መልኩ ቢጠናቀቅም ፤ ለውድድሩ ዝግጁ ይሆናል ወይ የሚለው ጉዳይ የገምጋሚ ቡድኑ ጥያቄ ነበር፡፡

በወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የሚገኙ ሁለት መለማመጃ ሜዳዎችን እና የአዲስ አበባ ስታዲየምን በመጎብኘት መዛኝ ቡድኑ ጉብኝቱን አጠናቋል፡፡

የካፍ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በሚያዚያ ወር በሚኖረው ስብሰባ የቻን 2020 ውድድርን ኢትዮጵያ ለማዘጋጀት ብቁ ናት ወይም ብቁ አይደለችም የሚለውን ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ ይጠበቃል፡፡

 

አጋራ
Profile photo of የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል ነው። በ1943 እ.ኤ.አ. የተመሠረተ ሲሆን፣ በ1953 እ.ኤ.አ. የፊፋ፣ እንዲሁም በ1957 እ.ኤ.አ. የካፍ (CAF) አባል ሆነ። ይህ አካል የብሔራዊ እግር ኳስ ሊግን እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድንን ያቀናጃል።

ምላሽ ይተው

Please enter your comment!
Please enter your name here